ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ሽፋንን 54 በመቶ ማድረስ ተችሏል

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 12/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ሽፋንን 54 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት÷ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት መርሃ ግብር በመቅረጽ እየተሰራበት ይገኛል።

በዚህም በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት በተከናወኑ ተግባራት 54 በመቶ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በተለያየ የኃይል አማራጭ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የፋይናንስ ተቋማትና የልማት አጋሮችም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የኃይል ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችል ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዚህም የፀሐይና የባዮ ጋዝ የቴክኖሎጂ ጸጋዎችን በመጠቀምና የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የከተማና የገጠር አካባቢዎችን የኢኮኖሚ ትስስር ማሰናሰል የሚያስችል ስኬታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

የፋይናንስ ተቋማትም ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የፀሐይ ኃይል ልማትን የሚያሳልጡ ግብዓቶችን እንዲያቀርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በሚገኘው የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂም በሀገር አቀፍ ደረጃ 240 ዋት የነበረውን የኃይል አቅርቦት ከ600 ዋት በላይ በማሳደግ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር የምስራች ሲሳይ÷ መንግስት የገጠሩን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የወሰደው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት የማሻሻያ እርምጃ የግል ድርጅቶችን እያበረታታ ነው ብለዋል።

በዚህም የማኅበሩ አባል የሆኑ 100 የግል ድርጅቶች በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሚሰሩ አማራጮችን ለገጠሩ ማህበረሰብ እያዳረሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ለፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ቴክኖሎጂን ለማቅረብና ለማከፋፈል የሚችሉበት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩንም ተናግረዋል።

የገጠሩን ማህበረሰብ የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል ያሉት የማኅበሩ ዋና ዳያሬክተር÷ የገንዘብ ተቋማትም በአነስተኛ ወለድ ለአርሶ አደሩ ብድር ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ የቢዝነስ ልማት ቡድን ማናጀር ገረመው ከፍያለው÷ ባንኩ ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በታዳሽ ኃይል የገንዘብ አቅርቦት ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የብድር አቅርቦት ስለሚፈልግ የልማት አጋሮችን ጥምር የብድር አቅርቦት አቅም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦት የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያመቻች የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም