ለ350 ወገኖች ብርሃን … - ኢዜአ አማርኛ
ለ350 ወገኖች ብርሃን …
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በበጎ ፈቃደኞች ተባባሪነት እና አሠራርን በማሻሻል ከታሰበው በላይ የ350 ወገኖችን የዐይን ብርሃን መመለስ ተችሏል።
ይህ አሃዝ ትንሽ ቢመስልም፤ ማየት አለመቻልን ማየት ወደ መቻል መመለስ በመሆኑ ከፍ ያለ ግምት ያሰጠዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 310 የዐይን ብሌን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገልጸዋል።
ሆኖም በበጎ ፈቃደኞች ተባባሪነት ከታቀደው በላይ 350 የዐይን ብሌኖችን በመሰብሰብ፣ በማዘጋጀት፣ በመመርመር፣ ለሕክምና ተቋማት በማሰራጨት ብርሃናቸውን መመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የዐይን ብሌን ከማሰባሰብ እና ብሌን ለመለገስ ቃል ከማስገባት አኳያ ያሳለፍነው በጀት ዓመት የተሻለ ነበር ሲሉም አቶ ሀብታሙ ለኢዜአ ተናግረዋል።
600 ሰዎች ከኅልፈት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ይገባሉ የሚል ግብ ተጥሎ በተከናወነው የትምህርትና ቅስቀሳ ሥራ 719 ሰዎች ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
እስከአሁን ሥራ ላይ ያለው የዐይን ባንክ በሀገሪቱ አንድ ብቻ መሆኑንና ተጨማሪ እንደሚያስፈልግም ጨምረው ጠቅሰዋል።
በዚህም መሠረት በጅማ ሪፈራል ሆስፒታል ተጨማሪ አንድ የዐይን ባንክ እስከ ፊታችን መስከረም ወር መጨረሻ ለመክፈት ጥረት እተደረገ ነው ብለዋል።
ለዐይን ባንክ የሚሆን የሥራ ቦታ ማዘጋጀትን ጨምሮ ግብዓት የማሟላትና የሰው ኃይል የማሰልጠን ሥራዎች መከናወናቸውንም ተነናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ450 በላይ የዐይን ብሌኖችን በማሰባሰብ፣ በማዘጋጀት፣ በመመርመርና በማሰራጨት ብርሃን ለመመለስ በዕቅድ መያዙንም ገልጸዋል።
እንዲሁም ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር 1ሺህ 500 ለማድረስ መታቀዱንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
የዐይን ባንክን ተደራሽነት ለማሻሻል በሁለት ክልሎች በሚገኙ ሁለት ትላልቅ ሆስፒታሎች ላይ የፍላጎትና የዝግጁነት ጥናቶችን ለማድረግ በዕቅድ መያዙንም አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል።
የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሻሻል፣ የሕዳር ወር የዐይን ብሌን ልገሳ ወር በሚል በንቅናቄ መመራቱ፣ ሰኔ ወርም ዓለም አቀፍ የዐይን ብሌን ልገሳ ቀን በንቅናቄ መከበሩና የተለያዩ ፎረሞችና ምክክሮች ላይ ስለጉዳዩ በስፋት ማስገንዘብ መቻሉ ለ2017 ከዕቅድ በላይ መሳካት ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
አሁንም የዐይን ብሌን ፍላጎት እና አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ ከኅልፈት በኋላ ብሌኑን በመለገስ የዐይን ብሌን ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቹ ብርሃን እንዲሆን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።