የመጅሊስ ምርጫው አካታችና ህዝበ ሙስሊሙ የነቃ ተሳትፎ ያደረገበት ነው - በአዲስ አበባ የመጅሊስ መራጮችና የምርጫ አስፈጻሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመጅሊስ ምርጫው አካታችና ህዝበ ሙስሊሙ የነቃ ተሳትፎ ያደረገበት ነው - በአዲስ አበባ የመጅሊስ መራጮችና የምርጫ አስፈጻሚዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የመጅሊስ ምርጫ አካታችና ህዝበ ሙስሊሙ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ ያደረገበት ታሪካዊ ምርጫ መሆኑን በአዲስ አበባ የመጅሊስ መራጮችና የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለጹ።
በመላው ኢትዮጵያ በመስጅድ ደረጃ የተካሄደው የዑለማ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና የስራ ማህበረሰብ ዘርፎች የመጅሊስ ምርጫ መጠናቋቁን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል።
ዛሬ በጠዋቱ መርኃ ግብር የምሁራንና የወጣቶች ከሰዓት ደግሞ የሴቶችና የሥራ ማህበረሰብ የመጅሊስ ምርጫ ተካሒዷል።
በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አቡ ሁረይራ መስጅድ በመገኘት ድምጻቸውን ከሰጡት መካከል ሰኢድ ኢብራሂም የምፈልገውንና ይወክለኛል ያልኩትን መርጫለሁ ብለዋል።
ለጥያቄዎቻችን ጆሮ የሚሰጥና ተግባራዊ እርምጃ የሚወስድ ስርዓት በመፈጠሩ ኩራትና ደስታ ተሰምቶናል ሲሉም ገልጸዋል።
ወጣት መሀሙድ ሙሌቤ በበኩሉ፤ ምርጫው ለረጅም ጊዜ ስንጠብቀው የነበረ ነው ያለ ሲሆን፥ ለማህበረሰቡ አንድነትና ለሀገር አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተወካዮችን በድምጻችን ለመምረጥ ዕድል ያገኘንበት ታሪካዊ ሁነት ነው ብሏል።
በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አቡ ሁረይራ መስጅድ ምርጫ ታዛቢ ዓሊ ሀሰን ሰኢድ በበኩላቸው ምርጫው ሥርዓቱን ጠብቆ ግልጽ በሆነ መንገድ መካሄዱን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የየካ ክፍለ ከተማ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ያሲን ሰኢድ በበኩላቸው ምርጫው ለቀጣይ ትልቅ ልምድ የተቀመረበት አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ምርጫው ለሙስሊሙ ማህበረሰብም ለሀገርም የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበርክቱ አመራሮች እንዲገኙ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የልደታ ክፍለ ከተማ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር እስማኤል ነስረዲን በዑስማን ኢብኑ አፋን መስጂድ/ሼክ ደሊል/ መስጂድ ምርጫው ስኬታማ በሆነ መንገድ ተካሂዷል ብለዋል።
የምርጫ ሂደቱ አካታችና የህዝበ ሙስሊሙ የነቃ ተሳትፎ የታየበት መሆኑንም ጠቁመዋል።