በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጅሊስ ምርጫ ፍትሃዊና አካታች በሆነ መልኩ ተካሂዷል

ወላይታ ሶዶ/አርባ ምንጭ ፤ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ፍትሃዊና አካታች በሆነ መልኩ መካሄዱን በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የክልሉ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አስታወቀ።

ከነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ሲካሄድ የቆየው የመጅሊስ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁም ተገልጿል።


 

የቦርዱ ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ ሹሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ 11 ዞኖች ባሉ 154 የምርጫ ማዕከላት የተካሄደው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊና አካታች ነበር።

ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በሁሉም የምርጫ ማዕከላት የኡለማዎች ምርጫ መካሄዱን አስታውሰው፣ በዛሬው እለትም  የወጣቶች፣ የሥራ ማህበረሰብ፣ የሴቶች እና የምሁራን ምርጫ መካሄዱን ተናግረዋል።

መራጮችም በአምስት ዘርፎች ከቀረቡ እጩዎች ህዝበ ሙስሊሙን ያገለግላሉ፣ በእውቀታቸው የተሻለ ይሰራሉ፣ ተቋሙንም ያሻግራሉ ያሏቸውን  በነጻነት የመረጡበት ሂደት እንደነበር ገልጸዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ያስን ከድር በበኩላቸው የመጅሊሱ ምርጫ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪካዊና ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በአራት ዘርፎች የተካሄደው የመጅሊስ የምርጫ ሂደት አካታች፣ ግልፅና ሰላማዊ እንደነበር ጠቁመው ምርጫው በተያዘው መርሀግብር መሰረት ተካሂዶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ለጠንካራ ተቋም ግንባታ አስተዋጽኦ የጎላ ነው ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪና የሴቶች ተወካይ ወይዘሮ ዘቢባ ሀጅ ከድር ናቸው።


 

በዚህ ታሪካዊ ምርጫ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ "በምርጫው የሚበጀንን መሪ በፍላጎታችን የመረጥንበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የምሁራን ተወካይ አቶ ካሊድ አህመድ በበኩላቸው ምርጫው ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባባት እና ኢ-ፍትሃዊ አካሄድን የሚፈታ ነው ብለዋል።


 

"በተጨማሪም የህዝበ ሙስሊሙን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሁም እኩልነትን እና የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ያሳደገ ነው" ሲሉም  አቶ ካሊድ አክለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም