የተከልናቸው የፍራፍሬ ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እንዲበቁ እንክብካቤ እናደርጋለን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የተከልናቸው የፍራፍሬ ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እንዲበቁ ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ እናደርጋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት አመራርና ሠራተኞች አስታወቁ፡።

የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ሸገር ከተማ መነ አቢቹ ክፍለ ከተማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን የአፕል ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡


 

የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች የዓለም ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡

እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የኢትዮጵያን የደን ሀብት ከማሳደግ በተጨማሪ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት አመራርና ሠራተኞች አሻራቸውን ማሳረፋቸው የሚኮሩበት ተግባር መሆኑንም አክለዋል።

በቀጣይ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የተተከሉ ችግኞች ፍሬ እንዲያፈሩ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እንደሚንከባከቡ ጠቁመዋል።


 

ከቤተሰቧ ጋር በችግኝ ተከላው የተሳተፈችው የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ሠራተኛ ገነት አዲሱ ችግኝ መትከል ለነገ ትውልድ ምቹ ሀገር መገንባት መሆኑን ተናግራለች፡፡

በዚህ መርሐግብር ልጆቿ መሳተፋቸው ነገ የአረንጓዴ አሻራ ጥቅምን በተጨባጭ ተረድተው በቀጣይ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ያስችላቸዋል ብላለች።

ሌላኛው የተቋሙ ሠራተኛ ዳዊት ሙሉጌታ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳተፍ ለትውልድ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው ገልጿል።


 

የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ከማስቻል በተጨማሪ አካባቢ ውብ እንዲሆን ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ መሳተፋቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት ደግሞ የመና አቢቹ ነዋሪ መቅደስ አግደው ናቸው።


 

የመነ አቢቹ ክፍለ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገመቺስ ዳንኤል በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ህብረተሰቡ፣ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች በርካታ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።

የተተከሉት ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ በማድረግ የአካባቢው ነዋሪ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም