ቀጥታ፡

የወጣቶችና ምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ግልጽ በሆነ መንገድ በስኬት መካሄዱን ታዝበናል - በአዲስ አበባ የተለያዩ መስጅዶች የምርጫ ታዛቢዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የወጣቶችና ምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ሂደት ግልጽ በሆነ መንገድ በስኬት መካሄዱን እንደታዘቡ በአዲስ አበባ በተለያዩ መስጅዶች የምርጫ ታዛቢዎች ገለጹ።

በአምስት ዘርፎች የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ነሐሴ 09 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በዑለማዎች ዘርፍ የድምጽ አሰጣጥ መርሃ ግብር መካሄድ መጀመሩ ይታዎሳል።

በዛሬው የነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም የወጣቶችና የምሁራን ዘርፎች የመጅሊስ ምርጫም በጠዋቱ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ-02 ሁዳ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ እና ሌሎች በርካታ መስጅዶች ተካሂዷል።

በከሰዓቱ መርሃ ግብር የሴቶችና የስራ ማኅበራት የመጅሊስ ምርጫ በየመስጅዶቹ ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።

የወጣቶችና የምሁራን ዘርፎች የመጅሊስ ምርጫ ታዛቢዎች በሁሉም ዘርፍ በተካሄደው ምርጫ የተሳተፉ አካላት ህዝበ ሙስሊሙን፣ ሀገርንና ሌላውን ማህበረሰብ በአንድነት በመምራት ይወክሉናል ያሏቸውን ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ መምረጣቸውን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ-02 የሁዳ መስጅድ የወጣቶችና ምሁራን ዘርፎች የምርጫ ታዛቢ ባህሩ ሀሰን እንደተናገሩት፤ መራጮች ይወክለኛል የሚሉትን በግልጽ ተሳትፎ መምረጣቸውን ታዝበዋል።

የምርጫ ሂደቱ ግልጽና አሳታፊ በሆነ አግባብ መካሄዱ የህዝበ ሙስሊሙን የዘመናት ምርጫችን በመስጅዳችን ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ስኬታማ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሀሰን መስጅድ የምርጫ ታዛቢ ሀጂ ሀሽቅ ሽኩር÷ የወጣቶችና ምሁራን ዘርፎች የመጅሊስ የምርጫ ሂደት መራጮች ነፃና ግልጽ በሆነ አግባብ ይወክለናል የሚሉትን አካል በስኬት መምረጣቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሀሰን መስጅድ የምርጫ ታዛቢ ሀጂ ኑሩ አወል÷ በምርጫ ሂደቱ ህዝበ ሙስሊሙ በግልጽ መምረጡን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ መስጅድ የምርጫ ታዛቢ ናስር ያሲን፤ ህዝበ ሙስሊሙ የሚፈልገውን አካል ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መምረጡን እንደታዘቡ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የ2017 ዓ.ም የዑለማዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የስራ ማኅበራት የመጅሊስ ምርጫ ላይ በ49ሺህ 92 መስጅዶች፣ 13 ሚሊዮን 151 ሺህ 889 ህዝበ ሙስሊም እየተሳተፈ ይገኛል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ ሂደቱን ጠብቆ የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም