አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና፣ በየጊዜው የማይለዋወጥ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና፣ በየጊዜው የማይለዋወጥ እና በኃያል ክህሎቱ ጥበብን ለዓለም መግለጥ የቻለ ታላቅ ሰው ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ(ረ/ፕሮፌሰር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ቴአትር ታላቅ ዐሻራውን ያሳረፈውና በሃገሩ ጉዳይ በጸና አቋሙ የሚታወቀው ታላቁ አርቲስት ደበበ እሸቱ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአርቲስት ደበበ እሸቱ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነ ጥበብ ታሪክ ታላቅ ዐሻራ ያሳረፈው አርቲስት ደበበ እሸቱ በማረፉ ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል።

ደበበ እሸቱ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ቴአትርና ፊልም ዕድገት ፋና ወጊ ከሆኑት ልሂቃን አንዱ መሆኑንና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ በጽናት እንድታሳካ በኪነ ጥበብ ተሰጥዖው ያበረከተውን ሚና ዘወትር ስናስታውሰው እንኖራለን ሲሉም ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ በአርቲስት ደበበ እሸቱ ኅልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው በኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደነበር አንስተዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከልጅነቱ ጊዜ ጀምሮ በጥበብ ዓለም በተዋናይነት፣ በደራሲነት፣ በአዘጋጅነት የሰራ እና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቤተ-ኪነ ጥበባት ወቴአትር(የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል) ውስጥም ዘመን የማይሽረው አሻራ ያኖረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አንጋፋው ከያኒ በኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኪነ-ጥበብ ሥራዎቹም ሀገሩን በጉልህ ያስጠራና ያስተዋወቀ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በውጭ ሀገር ተምረው ወደ ሀገራቸው በመመለስ ወደ አገልግሎት መስጠት ከገቡት መካከል በቀዳሚነት ስሙ የሚጠራ አርቲስት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከወዳጁ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን በብሔራዊ ቴአትር ሰፊ የጥበብ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከተጫወታቸው ተውኔቶች መካከልም እናት ዓለም ጠኑ፣ ያለአቻ ጋብቻ፣ ጠልፎ በኪሴን ጨምሮ የመንግስቱ ለማን እና የጸጋዬ ገብረ መድህን ታላላቅ የተውኔት ስራዎች ላይ መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ በቬኑሱ ነጋዴ እና ንጉስ ሊር ከተወነባቸው የትርጉም ተውኔት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከሀገር ውጭም በኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ መሳተፉን ተናግረዋል፡፡

በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ጥበብ፣ ኃይል፣ ተሰጥኦ፣ ባህል፣ ታሪክ ምልክቶችን የሚገልጡ ስራዎችን መስራቱንም አስታውሰዋል።

ለአብነትም ሆሊውድ ውስጥ 'ሻፍት ኢን አፍሪካ' የሚል ፊልምን ጨምሮ በሌሎችም ላይ መሳተፉን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ደረጃ የተዋንያን ማህበር በማቋቋም በመስራች ፕሬዚዳንትነት ጭምር የመራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ የመብት ተሟጋች እንደነበር አስታውሰው፤ ከያኒያን ሀገራቸውን መውደድ፣ ለሷም መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ለሀገር መቆምን በተግባር ያስተማረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ደበበ የዘመን መለዋወጥ የማይበግረው፣ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና አቋም የጸና መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅሩ ለወጣቶችም አርዓያ መሆን የቻለ ታላቅ የጥበብ ሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም