በክልሎቹ የመጅሊስ ምርጫ በስኬት ተጠናቋል

ሲዳማ/ ጅግጅጋ/አሶሳ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ፣ በሶማሌ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።

የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሼህ ኢስማኤል ሲራጅ እንዳሉት ላለፉት ሶስት ቀናት በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፉ የመጅሊስ ምርጫ በስኬት ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው የኡለማዎች ምርጫ ጀምሮ በዛሬው ዕለት የተከናወነው የምሁራን፣  የወጣቶች፣ የሴቶችና የስራ ማህበረሰብ ክፍሎች ምርጫ ፍትሃዊና አካታች ሆኖ መካሄዱን ገልጸዋል።


 

የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ አብዱልረሺድ አብዱላሂ በበኩላቸው   በክልሉ ከነሐሴ  9 እስከ 11 ቀን  2017 ዓም በኡለማዎች፣ በሴቶች፣ በወጣቶች፣ በምሁራንና በስራ ማህበረሰብ ዘርፎች የተካሄደው ምርጫ አሳታፊ ነበር።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተካሄደው የመጅሊስ ምርጫም በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሐጅ ጀማል ዑመር ተናግረዋል።


 

ላለፉት ሶስት ቀናት በክልሉ 566 መስጂዶች የተካሄደው ምርጫ አሳታፊ እንደነበር ሐጅ ጀማል ዑመር ገልጸዋል።

በኡለማዎች፣ በሴቶች፣ በወጣቶች፣ የሥራ ማህበር እና ምሁራን ዘርፍ በየመስጂዱ የተደረገው ምርጫ ነፃና አሳታፊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ተናግረው፣ ከፌዴራል መጅሊስ ጋር በመተባበር ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የክትትል ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ሁሉም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን እንዲሁም ህብረተሰቡ ላሳየው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም