የመጅሊስ ምርጫው የሚወክለንን አካል ፍትሐዊና ነፃ በሆነ አግባብ እንድንመርጥ እድል የፈጠረ ነው - የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ መራጮች - ኢዜአ አማርኛ
የመጅሊስ ምርጫው የሚወክለንን አካል ፍትሐዊና ነፃ በሆነ አግባብ እንድንመርጥ እድል የፈጠረ ነው - የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ መራጮች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የመጅሊስ ምርጫ ሂደቱ የሚወክለንን አካል ፍትሐዊና ነፃ በሆነ አግባብ እንድንመርጥ እድል የፈጠረ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የተለያዩ መስጅዶች ኢዜአ ያነጋገራቸው የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ መራጮች ገለፁ።
ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም በዑላማዎች ዘርፍ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ዛሬም ቀጥሎ የምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የሥራ ማህበረሰብ ምርጫ እየተካሄደ ነው።
በአዲስ አበባም በጠዋቱ መርኃ ግብር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ-02 ሁዳ እንዲሁም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ መስጅዶችን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ተካሂዷል።
የሁዳ መስጅድ ኢማምና የምሁራን ዘርፍ የምርጫ ተሳታፊ ሀሊድ በድረዲን የወጣቶችና ምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ሂደት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው ብለዋል።
የመጅሊስ ምርጫ ሂደቱ በዑለማዎች፣ በወጣቶች፣ በምሁራን በሴቶችና በስራ ማህበራት ዘርፍ በሁሉም መስጅዶች መካሄዱም ለህዝበ ሙስሊሙ አንድነትና ለኃይማኖታዊ አስተምህሮ መጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የሁዳ መስጅድ የምሁራን ዘርፍ የምርጫ ተሳታፊ መሐመዲን ነስሪን የምርጫ ሂደቱ አሳታፊና ግልጽ በሆነ አግባብ የሚወክላቸውንና በቀጣይም የተሻለ ስራ ይሰራልናል ያሉትን አካል መምረጥ የቻሉበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ምርጫው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን መስጅድ መራጭ የሆኑት ዶክተር ኡስማን መሀመድ ምርጫው ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ይበጀናል ያልነውን የመረጥንበት ነው ብለዋል።
ሌላዋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን መስጅድ መራጭ ነጅቢያ ዘይኑ በበኩላቸው ስለተመራጮች ተገቢውን ገለፃ ተደርጎላቸው በተቀላጠፈ አግባብ ምርጫውን ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
የለሚ ኩራ ጎሮ አንቢያ መስጅድ የወጣቶች ዘርፍ መራጭ ሙከረም ሃምዛ ምርጫው አሳታፊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክሉትን የመረጡበት መሆኑን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ መስጅድ የምሁራን መራጭ የሆኑት ሚልካ ኢብራሂም ህዝበ ሙስሊሙን በአግባቡ ይመራሉ ያሏቸውን አካላት በግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ መምረጣቸውን ተናግረዋል።