ቀጥታ፡

የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ግልጽና አሳታፊ በሆነ አግባብ ተከናውኗል - በአዲስ አበባ የተለያዩ መስጅዶች የምርጫ አስፈፃሚዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ግልጽና አሳታፊ በሆነ አግባብ መከናወኑን በአዲስ አበባ የተለያዩ መስጅዶች ያነጋገርናቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለፁ።

ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በዑለማዎች ዘርፍ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ዛሬም ቀጥሎ የምሁራን፣ የወጣቶች፣ የሴቶችና የሥራ ማህበረሰብ ምርጫ እየተካሄደ ነው።

በዚህም በጠዋቱ መርኃ ግብር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ-02 ሁዳ እንዲሁም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ መስጅዶችን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ተካሂዷል። 


 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ ሁሴን ላለምዳ እንዳሉት ምርጫው ግልፅና አሳታፊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው። 

በዛሬው እለት በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የምሁራንና ወጣቶች ምርጫ መካሄዱን ገልፀው ከሰዓት ደግሞ የሴቶችና የስራ ማህበራት ምርጫ እንደሚካሄድ አብራርተዋል። 

በተለያዩ መስጅዶች በመዘዋወር የምርጫውን ሂደት መመልከታቸውን ተናግረው በዚህም መራጩ ግልፅ በሆነ መንገድ እየመረጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ዶክተር ኢብራሂም ሙሉሸዋ በበኩላቸው ምርጫው ሙስሊሙን ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ ነው ብለዋል። 


 

ሁሉንም ህብረተሰብ ያሳተፈ ተቋም መመስረት በሚያስችል መልኩ ህብረተሰቡ ግልፅ በሆነ አግባብ ድምፁን በመስጠት እየተሳተፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሁዳ መስጅድ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሙክታር አሕመድ የምርጫው ሂደት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲጠይቀው የነበረውን ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው ብለዋል። 

የምርጫ ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች ጭምር ለህዝበ ሙስሊሙ ቅስቀሳ በማድረግ ስኬታማ ምርጫ እንዲካሄድ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ መስጅድ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ጀሚላ ሰኢድ ምርጫው ህብረተሰቡ በአቅራቢያው አመራሮቹንና ተወካዮቹን እንዲመርጥ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሐሰን መስጅድ የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ አንሳር ጁሃር ምርጫው አሳታፊና ህብረተሰቡ ይበጀኛል ያለውን ነፃ በሆነ መንገድ የመረጠበት ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ሂደቱን ጠብቆ የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም