ቀጥታ፡

የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ማህበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ማህበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

አቅመ ደካማ ወገኖችን የመደገፍ ሀገራዊ በጎ እሴትን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁሟል።

አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ሸገር ከተማ መና አቢቹ ክፍለ ከተማ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ እናቶች ደግሞ ለእርባታ የሚሆኑ በጎች ድጋፍ አድርጓል፡፡


 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ በወቅቱ እንደገለጹት አቅመ ደካማ እና በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝና መደገፍ የሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ግዴታ ነው፡፡

የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤትም ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተማሪዎች ቁሳቁስ እንዲሁም የእርባታ በጎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


 

ድጋፉ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማገዝና እናቶች ሰርተው እንዲለወጡ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡።

በቀጣይም አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል  አስታውቀዋል፡፡ 


 

የሸገር ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ጫሊ በበኩላቸው ተቋሙ ለተማሪዎችና ወላጆች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ድጋፍ ማበርከቱን አመልክተዋል፡፡

ድጋፉ ህጻናቶች ጠንክረው በመማር እናቶች ደግሞ በርትተው በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡


 

በሸገር የመና አቢቹ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አዲሱ ከበደ የመተባበርና የመደጋገፍ እሴትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡


 

ድጋፍ የተደረገላቸው ጥሩነሽ በቀለ እና ስንታየሁ ደበሌ የተደረገላቸው ድጋፍ ኑሯቸውን ለመለወጥ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም