በጣና ሀይቅ ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የሀይቁን ዘላቂ ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- በጣና ሀይቅ ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የሀይቁን ዘላቂ ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።

የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን የጣና ኃይቅን ህልውና መጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሆቴሎች፣ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በባህርዳር ከተማ መክሯል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት የክልሉም ሆነ የኢትዮጵያ ጌጥ የሆነውን የጣና ሃይቅ መጠበቅ የሁሉም አካላት ሃላፊነት ነው።

በተለይም በሃይቁ ዙሪያና አቅራቢያ እንደ ሆቴል፣ ሪዞርትና ሌሎች የልማት ስራዎች የሚሰሩ አካላት ስራቸውን ሀላፊነት በተሞላበት መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታቸውን በማዘመን፣ የሃይቁን ወሰን ባለመጋፋትና የሀይቁን ደህንነት በሚያረጋግጥ መልኩ ስራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በሀይቁ ዙሪያ የሚከናወኑ ልማቶች ህግና መመሪያን ባከበረ መልኩ መሆን እንዳለበትም መክረዋል።


 

የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ኃላፊ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው በጣና ሃይቅ ላይ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻን በመልቀቅና ድንጋይ እየሞሉ በመደልደል የሀይቁን ህልውና የሚፈታተኑ አካላት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

ባለስልጣኑ በቀጣይ የሀይቁን ደህንነት የሚያስጠብቁ ህጎችንና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ህጋዊ እርምጃ  እንደሚወስድ አመላክተውል።

የዛሬው ውይይትም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የወጡ መመሪያዎችንና ደንቦችን በመገንዘብ ኃላፊነቱንና ግዴታውን አውቆ የልማት ስራዎችን እንዲያከናውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉና ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም