ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ መስጅዶች የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ መስጅዶች የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ተካሂዷል።

ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም በዑለማዎች ዘርፍ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ዛሬም ቀጥሎ የምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የሥራ ማህበረሰብ ምርጫ እየተካሄደ ነው።


 

በአዲስ አበባም በጠዋቱ መርኃ ግብር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአል ኢማም ሃሰን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ-02 ሁዳ እንዲሁም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ አንቢያ መስጅዶችን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ተካሂዷል።


 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ ሁሴን ላለምዳ እንዳሉት ምርጫው ግልፅና አሳታፊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው።

በዛሬው እለት በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የምሁራንና ወጣቶች ምርጫ መካሄዱን ገልፀው ከሰዓት ደግሞ የሴቶችና የስራ ማህበራት ምርጫ እንደሚካሄድ አብራርተዋል።

በተለያዩ መስጅዶች በመዘዋወር የምርጫውን ሂደት መመልከታቸውን ተናግረው በዚህም መራጩ ግልፅ በሆነ መንገድ እየመረጠ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።


 

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ሂደቱን ጠብቆ የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም