ኢንስቲትዩቱ በውኃ ቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኃይል ግንባታ ሀገራዊና ቀጣናዊ አቅም እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ በውኃ ቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኃይል ግንባታ ሀገራዊና ቀጣናዊ አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውኃ ቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኃይል ግንባታ ሀገራዊና ቀጣናዊ አቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታመነ ኃይሉ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከአስራ አምስት በላይ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት በውኃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ውጤታማ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በዚህም የስልጠና ልህቀት ማዕከል መሆን የሚያስችለውን የአቅም ግንባታ እና ሎጂስቲክስ የማሟላት ስራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታመነ ኃይሉ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የውኃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰሩ በሚገኙ ስራዎች የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
አርሶ አደሩን ጨምሮ ዜጎች በአነስተኛ ወጪ ውኃን ከከርሰ ምድር እንዲያገኙ ለማስቻል ቀላልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ አገልግሎቱን በማስፋት ዘርፉ የሚፈልገውን ድጋፍ ለማፋጠን እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የውኃ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በየጊዜው ተግባራዊ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም እየገነባ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
ሰልጣኞች በየክልላቸው የተለያዩ ጥገናዎችን በራስ አቅም በማካሄድ ለውኃ ተደራሽነት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በውኃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሀገር አልፎ ቀጣናዊ አቅምን ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው የተናገሩት፡፡
በዚህም ከአስራ አምስት በላይ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አንስተው በዚህም እስካሁን ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ 218 ባለሙያዎች በተለይ በከርሰ ምድር የውኃ ቁፋሮ ዙሪያ ልዩ ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣናው የውሃ ቴክኖሎጂ ምርምርና የስልጠና ልህቀት ማዕከል ለመሆን ሎጂስቲክስ የማሟላት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በኢንስቲትዩቱ ስልጠና እየወሰዱ ያገኘናቸው ፍቅረ ዮሐንስ አሰፋ እና አሰድ ሙሃመድ ስልጠናው በተግባር የተደገፈ በመሆኑ በቂ እውቀት እያገኙበት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በስልጠናው ያገኙትን ሙያዊ ክህሎት በመጠቀም በአካባቢያቸው የውኃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡