የክልሉን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ሠመራ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የክልሉን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋት አቅም የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድን በተመለከተ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የገቢ ጽህፈት ቤቶች አመራሮች በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ የክልሉን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋት አቅም የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በተያዘው በጀት ዓመት 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተው ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብና አቅምን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አወል አብዱ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ገቢን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አንስተው በዚህም መሰረት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
የክልሉን በጀት በሚሰበሰበው ገቢ ለመሸፈን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ለስኬታማነቱ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ወረዳዎች፣ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ምስጋና እና ዕውቅና ተሰጥቷል።