የሕዳሴው ግድብ ለፍጻሜ መብቃት በትብብር ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ ለፍጻሜ መብቃት በትብብር ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው
ዲላ/አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ):-የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ መብቃት በትብብር ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም ማሳካት እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የዲላና አርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ እና አርባ ምንጭ ከተሞች ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ መድረስ በመተባበር የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማሳካት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው።
ከዲላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፀጋነሽ ሰለሞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ10 ጊዜ በላይ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራቸውን ያሳረፉበትና ተባብሮ በመስራት በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሕዳሴው ተሞክሮ ሌሎች ልማቶችንም በአንድነት ማሳካት ይገባናል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ከሀይል አቅርቦት ባለፈ ልማትን በማቀላጠፍ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ያለው ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት ተገኝ ኃይሌ ነው።
በትብብር መስራት ለስኬት እንደሚያበቃ የሕዳሴው ግድብ አንድ ማሳያ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ፣ በቀጣይም በሰላም ግንባታ እና በሌሎች የልማት መስኮች ላይ በመረባረብ ሀገራዊ የእድገት ጉዞን ማፋጠን እንደሚገባ ገልጿል።
በኢትዮጵያዊያን ትብብር ተጀምሮ ለፍጻሜ የደረሰው የሕዳሴው ግድብ በህዝብ ላይ የይቻላል መንፈስን ማስረጹን ጠቁሞ፣ ለግድቡ ኢትዮጵያዊያን ያሳዩት ትብብርና አንድነት ሌሌች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በአብሮነት ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብሏል።
የሕዳሴው ግድብ የአንድነታችን አርማ ነው ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪው ኮማንደር ተፈራ ማህተሜ ናቸው።
በግንባታው ሂደት በቦንድ ግዥ፣ የአካባቢዎችን ነዋሪዎች በማስተባበርና በሀሳብ ሲደግፉ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የዛሬው ትውልዱ የልማት አርበኝነቱን ያረጋገጠበት በመሆኑ በቀጣይም ሕብረትና አንድነትን በማጠናከር ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት ይገባል ብለዋል።
ሌላኛዋ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ላቾሬ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መላው ህዝብ በአንድነት ታሪክ የሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የትውልዱ ደማቅ ታሪክ መሆኑን ገልጸው፣ "በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት ለግድቡ ግንባታ ያሳየነውን ትብብር አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል" ብለዋል
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቅርቡ ለምረቃ እንደሚበቃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።