የተቀናቃኞቹ የማንችስተር ዩናይትድ እና የአርሰናል ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ተቀናቃኞቹን ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናልን አገናኝቷል።

 የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ሲገናኙ የአሁኑ ለ245ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 244 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 99 ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል 90 ጊዜ ድል ሲቀናው 55 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታዎቹ ማንችስተር ዩናይትድ 366 ግቦችን ሲያስቆጥር አርሰናል 348 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪካዊ ተቃናቃኞች የሚባሉ ቡድኖች ሲሆኑ ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1894 ነበር። 

በዚሁ ጨዋታ ቡድኖቹ ሶስት አቻ የተለያዩ ሲሆን ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ130 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል። 

በተለይም እ.አ.አ በ1990ዎቹ ማብቂና በ2000 መጀመሪያ ላይ የባላንጣነት ስሜታቸው እያደገ መጥቷል።  

ማንችስተር ዩናይትድ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን እንዲሁም አርሰናል በአርሰን ቬንገር በሚመሩበት ወቅት የነበራቸው ፉክክር የሚዘነጋ አይደለም። 

ማንችስተር ዩናይትድ 20 ጊዜ፤ አርሰናል 13 ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስተዋል። 

ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዓመት 15ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ መጥፎ የሚባል የውድድር ዓመት ሲያሳልፍ በአንጻሩ አርሰናል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በሩበን አሞሪም የሚሰለጥነው ማንችስተር ዩናይትድ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ማቲያስ ኩንሃ፣ ብሪያን ምቡዌሞ እና ቤንጃሚን ሼሽኮን በማስፈረም የማጥቃት አቅሙን አጠናክሯል።

የአጥቂው መስመር መጠናከርና በቅድመ ውድድር ዝግጅት ቡድኑ ላይ የታዩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ማንችስተር ዩናይትድ ቤት በመልካምነት የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው። 

ቡድኑ ተሰርቶ ያላለቀ እና በሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑ ገና ብዙ እንደሚቀረው የሚገልጹም አሉ።

የማይክል አርቴታው አርሰናል በበኩሉ ቪክቶር ዮኮሬሽ፣ ማርቲን ዙቢሜንዲ፣ ኖኒ ማዱዌኬ፣ ክርስቲያን ኖርጋርድ፣ ክርስቲያን ሞስኩዌራ እና ኬፓ አሪዛባላጋን በማስፈረም የቡድን ስብስብ ጥልቀቱን አስፍቷል።

በሁሉም የመጨዋቻ ክፍሎች ላይ አቅሙን የጨመረው አርሰናል የአዲስ ፈራሚዎች ሊወስድባቸው የሚችለው ከቡድን ጋር የመወሃጃ ጊዜ እና የፈጠራ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ማነስ ፈተና ሊሆንበት ይችላል።

በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አርሰናል ያሸንፋል የሚሉ ግምቶች ቢያመዝኑም ማንችስተር ዩናይትድ በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። 

የ43 ዓመቱ ሳይመን ሁፐር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም ቼልሲ ከክሪስታል ፓላስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ከብሬንትፎርድ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም