የግንባታ ባለሙያዎች የደህንነት መጠበቂያ ግብዓቶች አጠቃቀምን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የግንባታ ባለሙያዎች የደህንነት መጠበቂያ ግብዓቶች አጠቃቀምን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2017(ኢዜአ)፡- የግንባታ ባለሙያዎች የደህንነት መጠበቂያ ግብዓቶች አጠቃቀምን ማጠናከር የሚያስችል የቁጥጥር መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ክትትልና ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር በረከት ተዘራ ለኢዜአ እንደገለጹት በግንባታ ስራዎች ላይ በግንዛቤ ክፍተት፣ ለደህንነት መጠበቅ ጉዳይ ትኩረት ባለመስጠትና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ አደጋዎች ይከሰታሉ።
በግንባታ ስራዎች ላይ የደህንት መጠበቂያ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ስለ ደህንነት መጠበቅ በየዕለቱ የሚያስተምር ባለሙያ "ሴፍቲ ኢንጂነር" እንዲኖር አስገዳጅ የሚያደርግ መመሪያ በህግ ማዕቀፉ መካተቱን ተናግረዋል።
የስራ ተቋራጮች የስራ ደህንነት መጠበቂያ ግብዓቶችን በግንባታ ወጪ ውስጥ ማካተትን የሚያስገድድ ህግ መኖሩንም አክለዋል።
ሆኖም እነዚህን ህጎች ተግባራዊ የማድረግና ለደህንነት ቅድሚያ የመስጠት ልምዱ አነስተኛ ነው ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር በረከት ገለጻ በዘርፉ አዳዲስ ሰዎች በየወቅቱ የሚቀላቀሉ በመሆኑ ስለ ደህንነት መጠበቅ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ የዕለት ከዕለት ተግባር መሆን አለበት።
ይህንን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ህጉን ባልተገበሩት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የቁጥጥር መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ኢንጂነር በረከት እንደተናገሩት የግንባታ ዲዛይን ፍቃድ በሚሰጥበት ወቅት የግንባታ ቦታዎች ከአደጋ ነጻ መሆናቸውን የማረጋገጥና የግንባታው ሂደት በምን መልኩ እንደሚከናወን ከደህንነት አንጻር እንደሚታይ ጠቁመዋል።
በቅድመ ግንባታ ወቅት የተቀመጡ የደህንነት ሰርዓቶች መተግበራቸውንም በግንባታው ወቅት በአካል የማረጋጋጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለስልጣኑ ከሚያደርገው ክትትል በተጨማሪ ህብረተሰቡ አደጋዎችን መጠቆም የሚችልበትና ሌሎች አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የስልክ መተግበሪያ የማበልጸግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አህመድ መሃመድ በበኩላቸው በግንባታ መሳሪያዎች ጥራት መጓደል፣ የደህንነት መጠበቂያዎችን ባለመጠቀምና በሌሎች ምክንያቶች አደጋዎች በስፋት ይከሰታሉ ብለዋል።
አደጋዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው በበጀት ዓመቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ የአደጋ መከላከል ስራዎች መጠናከራቸውን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
ግንባታዎች የደህንነት መጠበቂያ ግብዓቶች ሳያሟሉ እንዳይጀመሩ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ በመድረስ የቁጥጥር ስራው ተጠናክሯል ብለዋል።
በከተማ ደረጃ ኮሚቴ በማቋቋም በተደረገው ቁጥጥር ግብዓቶችን ያላሟሉ የግንባታ ስራዎች አሟልተው እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የቁጥጥር ስራዎች በመጠናከራቸው የስራ ላይ አደጋን በመቀነሱ በኩል ለውጦች ተገኝተዋል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።