ቀጥታ፡

ክረምት እና ጤና

ዝናብና ቅዝቃዜን በሚያስተናግደው ባለንበት የክረምት ወቅት በተደጋጋሚ ለተለያዩ በሽታዎች  ተጋላጭ የመሆን አጋጣሚ ስለሚኖር የመከላከያ እርምጃዎችን አጥብቆ መተግበር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በተለይም ወቅቱ ህፃናት ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በቤት ውስጥና በመኖሪያ አካባቢ የሚያሳልፉ በመሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል።

ማዮ ክሊኒክ በክረምት ወቅት የሚከሰቱ በሽታዎችን እንዴት መከላከል እንችላለን? በሚል በድረገጹ ባወጣው የጥንቃቄ መልዕክት ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል ይገልጻል፡፡

በክረምቱ ወቅት ለፀሀይ የሚኖረን ተጋላጭነት አነስተኛ በመሆኑ በሽታ የመከላከል ስርዓትን ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆነው የቫይታሚን ዲ መጠን መቀነስ አንደኛው የጤና ችግር መሆኑንም አትቷል፡፡

በሌላ በኩል በክረምት ወቅት ከሚከሰቱ ህመሞች መካከል የመተንፈሻ አካል ህመም እና እንደ ኮሌራ ያሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዲሁም ከምግብ ብክለት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ በሽታዎች ተጠቃሽ መሆናቸውም እንዲሁ።

ጉንፋንና ብሮንካይትስን ጨምሮ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች በቀዝቃዛ ወራት በብዛት እንደሚከሰቱም በመልዕክቱ ተጠቁሟል፡፡

ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ቫይረስ በቀላሉ እንዲሰራጭና ሰውነታችን የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡

ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ጉንፋንን በቀጥታ ባያመጣም ለቫይረሶች መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ነው ድረገጹ ያስነበበው፡፡ በክረምት ወቅት የሚከሰተው ጉንፋን እና የተለያዩ የመተንፈሻ አካል ህመሞች አብዛኛውን ጊዜ በአየር ጸባይ ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ መሆናቸውን በማሳያነት አቅርቧል።

ነገር ግን ቀዝቃዛ የአየር ጸባይ ብቻ ሳይሆን በክረምት ወቅት ሰዎች በቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ስለሚያሳልፉ፣ ቫይረሱ በማሳል፣ በማስነጠስ ወይም በጋራ መጠቀሚያ ቦታዎች ንክኪ በቀላሉ ሊተላለፍ ስለሚችል መሆኑንም አመላክቷል።

በመሆኑም ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ቫይረሶች በቀላሉ እንዲሰረጩ እና በሽታ የመከላከል ስርዓታችን እንዲዳከም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ሰዎች በክረምት ወቅት መደረግ ያለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቀምጧል። እነርሱም ፦

1. ከቤት ውጪ በሚሆኑበት ወቀት ዣንጥላ እና የዝናብ መከላከያ አልባሳትን መጠቀም፤

2. አመጋገብን ማስተካከል፡- ለክረምት ተስማሚ የሆኑ የተመጣጠነና ገንቢ ምግብ ለመመገብ መሞከር። ምግብ በሚያዘጋጁበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም በቫይታሚን ሲ እና ዲ የበለፀጉ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን መመገብ፤

3. ትኩስ መጠጦችን መውሰድ፦ ይህም በሰውነታችን ውስጥ በሙቀትና ቅዝቃዜ መቀያየር ምክንያት የሚከሰቱ ድንገተኛ ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን፤

4. ንፅህናን መጠበቅ፦ በክረምት ወቅት ንፅህና በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና መታጠብ ራስን ከኢንፌክሽን ለመጠበቅ እንደሚረዳ፤

5. ውሃ በብዛት መጠጣት፦ በክረምቱ አየር ፀባይ ምክንያት የሰውነታችን የውሃ መጠን በተፈጥሮ ሊቀንስ ስለሚችል የመጠማት ስሜት ባይኖር እንኳን ውሃ መጠጣት እንደሚመከር፤

6. በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት፣ በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ትልቅ ጥቅም እንዳለው መረጃው ያሳያል፡፡ እንዲሁም ከክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ የሚመጣን የስሜት መታወክ ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና እንዳለው፤

7. በእርጥበት ምክንያት የሚከሰቱ በቤት ግድግዳ ላይ የሚፈጠሩ ሻጋታዎችን ማስወገድ፡- ይህም በመታጠቢያ ቤትና እርጥበት ያላቸው ቦታዎች ላይ በብዛት ይፈጠራል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእርጥበት እና በሻጋታ የመጎዳት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ እንሚገባ፤

በክረምት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ህመሞችን በማወቅ እና የጥንቃቄ መንገዶችን በመከተል እራስንና ቤተሰብን ከበሽታ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም