የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ክፍያ ፈፀመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ክፍያ ፈፀመ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ።
ባንኩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየጊዜው ለደንበኞቹ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማስተናገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
በዚህም መሰረት በዛሬውም ዕለት ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ለባንኩ የቀረቡ የውጭ ምንዛሪ የደንበኞቻችን ማመልከቻዎችን ሁሉንም በማጽደቅ የ420 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ዓይነቶች ለተለያዩ ፍላጎቶች ፈቅዷል ሲል ገልጿል።
የዛሬው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ከሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ከተፈቀደው ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ በባንካችን ለ1 ሺህ140 ደንበኞች 541 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሪ ተፈቅዷል ብሏል።
ይህም የተሰጠው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ከነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ጋር በተያያዘ በየቀኑ ከሚሰጠው መደበኛ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በተጨማሪ የተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
ባንኩ ከጁላይ 1 ቀን 2025 ጀምሮ ለገቢ ንግድና ለአገልግሎት ክፍያዎች በአጠቃላይ 1 ነጥብ 034 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ፈፅሟል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደንበኞቹ ፍላጎት እና አገር ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ጋር በማጣጣም ለውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በመደበኛነት ምላሽ መስጠቱን እንደሚቀጥልም ባንኩ አስታውቋል።