ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የመጅሊስ ምርጫ የምሁራንና የወጣቶች ድምፅ አሰጣጥ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል

ጋምቤላ፤ ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ የምሁራንና የወጣቶች ዘርፍ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ መጠናቀቁን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አስታወቀ። 

የቦርዱ ሰብሳቢ ሐጂ አማር አህማድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት የተጀመረው ሀገረ አቀፍ የመጅሊስ ምርጫ ዛሬ የምሁራንና የወጣቶችን ዘርፍ ምርጫ በማከናወን በስኬት ተጠናቋል።

በክልሉ ሀገር አቀፉ የመጅሊስ ምርጫ ሁሉንም ህዝበ ሙስሊም ባሳተፈ መልኩ ነፃና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመጅሊሱ ምርጫ በትናንትናው እና በዛሬው ውሎ የኡለማዎች፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና የምሁራን ዘርፍ የምርጫ ሂደቶች ተከናውነው መጠናቀቃቸውን ጠቁመው በነገው ዕለትም የስራ ማህበራት ዘርፍ ምርጫ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው የዘንድሮው ምርጫ ዘመናዊ ከመሆኑም ባለፈ ሁሉንም ያሳተፈ በመሆኑ መጅሊሱ ጠንከራና ብቃት ያላቸውን አመራሮች ሊያገኝ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል። 

የክልሉ የኡለማዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊና የምርጫ ቦርዱ አማካሪ ሼህ እንድሪስ ሁሴን የዘንድሮው የመጅሊስ ምርጫ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ አሳታፊና ፍትሀዊነትን የተላበሰ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይህም ጠንካራ መጅሊስ ለመመስረትና ህዝበ ሙስሊሙን በተሟላ መልኩ ለማገልገል የሚያስችል ተቋም ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም