የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ክሕሎት እና የዳበረ ስብዕና ያለው ወጣት ለማፍራት እያስቻሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ክሕሎት እና የዳበረ ስብዕና ያለው ወጣት ለማፍራት እያስቻሉ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የተከፈቱት የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ክሕሎት እና የዳበረ ስብዕና ያለው ወጣት ለማፍራት እያስቻሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር "በለውጡ የተለወጠ ወጣት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት ፌስቲቫል ተካሄዷል።
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሒም ናስር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የወጣቶች ሚና የላቀ ነው።
ከተማ አስተዳደሩም ወጣቶች በአስተሳሰብ፣ በአካልና በስብዕና የዳበረ እንዲሆኑ የስብዕና መገንቢያ ማእከላትን ማጠናከር አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ማብቃት ዳይሬክተር አቶ ንብረት ይሁኔ በበኩላቸው፤ ወጣቱ ትውልድ ብቁ የሆነ ክሕሎትን ከማዳበር ባሻገር በአስተሳሰብ የተሻለ ቁመና እንዲኖረው እየተሰራ ነው።
ከዚህ ውስጥም ወጣቶች ስብዕናቸውን የሚገነቡበትና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት 114 ማዕከላት ተገንብተው የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።፡
በዛሬው እለት የተካሔደው ፌስቲቫል በማዕከላቱ የወጣቶችን ተሳትፎና ተሞክሮ ለማስተዋወቅ እና ልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል።
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አበበ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው ባሉት 10 የሚደርሱ የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በርካታ ወጣቶች አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አብራርተዋል።
የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ወጣት ቤተልሔም ሙሉጌታ፤ በቴኳንዶ ስፖርት መሳተፏን ገልጻ፤ በቀጣይም ሀገሯን በመወከል በዘርፉ የመወዳደር ሕልም እንዳላት ነው የገለፀችው።
የሀገርን ባሕልና እሴት ለማስተዋወቅ በባሕላዊ ውዝዋዜ ዘርፍ እየተሳተፈች መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ወጣት ሀና የኋላእሸት ናት።
በፌስቲቫሉ የወጣቶች ባህላዊና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ ሰርከስ ትርኢት፣ የቴኳንዶና የካራቴ ስፖርት፣ ቲያትር እና ክብደት ማንሳት ትርኢቶች ቀርበዋል፡፡