እሴት የተጨመረበት ዲጂታል የፖስታ ሳጥን አገልግሎት በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦ዘመኑን የዋጀ የፖስታ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እሴት የተጨመረበት የዲጂታል ፖስታ ሳጥን በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ከ130 ዓመታት በላይ በተሻገረ የረጅም ዘመን ታሪኩ እንደ አንጋፋነቱ ማደር ተስኖት ማትረፍ ቀርቶ እዳውን ለመክፈል ሲቸገር ቆይቷል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባደረገው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ከተበረከተላቸው አምስት ተቋማት መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ በእዳ የተዘፈቀ እና በመዘግየት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ፖስታ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስም ካላቸው ተስፋ ሰጭ ተቋማት መሰለፍ መቻሉን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ተቋሙ በቴክኖሎጂና አሰራር ችግር ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ መወጣት ባለመቻሉ በተደረገ ጥቅል ሪፎርም በፈጣን እድገት ምህዋር ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ዓለም አቀፉ የፖስታ ሕብረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ተብሎ ሽልማት ተበርክቶለታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ከጥንት ጀምሮ ከሚታወቅባቸው አገልግሎቶች መካከል የፖስታ ሳጥን አንዱ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ አገልግሎቱን እሴት በመጨመር በዲጂታል ስርዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡

ስለሆነም ደንበኞች ዘመናዊና የተሟላ የዲጂታል ፖስታ ሳጥን (vertual post box) አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ፖስታ ሳጥን ደንበኞች አድራሻቸውን ሲቀይሩ በፍጥነት የሚያሳውቅ፤ ተቋሙም ያሉበትን ቦታ በትክክል አውቆ መልዕክቱን በፍጥነት ማድረስ የሚችልበት አሰራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደንበኞች የተላከላቸውን መልዕክት በስልካቸው የሚከታተሉበት እንዲሁም አድራሻቸውን /KYC/ በሚቀይሩበት ወቅት ባሉበት ቦታ የሚያደርስ ዘመናዊና ፈጣን አገልግሎት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ፖስታ ሳጥን ለደንበኞች ተጨማሪ ክፍያ የማይጠየቅባቸው ሌሎች ጥቅል አገልግሎቶችን መያዙን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ሰዎች በእለት ከእለት ኑሯቸው የሚጠቀሟቸው አገልግሎቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎቱ የመጨረሻ የጥራት ማረጋገጫ ፍተሻ ላይ መድረሱን በመጥቀስ፤  እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም መጨረሻ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም