ቀጥታ፡

ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር አድማስ በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት-አምባሳደር ቴቤሌሎ ቦአንግ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 10/2017 (ኢዜአ)፡-ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ የሁለትዮሽ ትብብሯን በተለያዩ መስኮች የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር ቴቤሌሎ ቦአንግ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቦትስዋና አምባሳደር ቴቤሌሎ ቦአንግ ሀገራቱ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የሁለትዮሽ ትብብሩ የህግ የበላይነትን በማክበር፣በአፍሪካ አንድነት እና የባለብዙ ወገን ማዕቀፍን ጨምሮ ሀገራቱ በሚጋሯቸው የተለያዩ እሴቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ ሁለቱ ሀገራት በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጽኑ የሆነ የጋራ ቁርጠኝነት አላቸው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል የሆኑት ሁለቱ ሀገራት በአህጉሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

አምባሳደር ቦአንግ ኢትዮጵያ በቀጣናው በተለይም በሶማሊያ እያከናወነች ያለው የሰላም ማስከበር ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፥ ቦትስዋና ኢትዮጵያ በቀጣናው ላላት የመሪነት ሚና ድጋፏን እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ሀገራቱ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ በተለያዩ የባለብዝሃ ወገን የትብብር መድረኮች በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ግብርና እያደገ የመጣው ትብብር ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው፥ ሀገራቱ በግብርና ልማት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ዝግጅት እያጠናቀቁ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ቦትስዋና ከፍተኛ ጥራት ባለው የስጋ ምርት እና የእንስሳት ጤና አገልግሎት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል እንደምትፈልግ የገለጹት አምባሳደሩ፥ የቁም እንስሳት እርባታና የሰብል ምርት ሀገራቱ ሊሰሩባቸው የሚችሉ መስኮች መሆናቸውን ነው ያነሱት።

በዓለም አቀፉ የእንስሳት ጤና እና መድኃኒቶች አምራች ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ያለው የቦትስዋና የክትባት ኢኒስቲትዩት የኢትዮጵያን የቁም እንስሳት ጤና ኢኒሺቴቮችና የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጥረቶች መደገፍ የሚችልበት አማራጭ እንዳለም ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በአፈር መረጃ ካርታ እና በቆዳ ኢንዱስትሪ ያላትን ለውጦች ያደነቁ ሲሆን ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪና የግብርና እሴት ሰንሰለቶች ተሞክሮ መቅሰም እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቦትስዋና ጋቦሮኒና ማውን ከተሞች የሚያደርገው በረራ የሀገራቱን የባህል፣ ቱሪዝም እና የንግድ ትብብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

ሀገራቱ በዘላቂ ልማት፣ ሰላም እና ብልጽግና አፍሪካዊ ተምሳሌት የሆነ ትብብር እየገነቡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1990 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እ.አ.አ በ2017 አጠቃላይ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የጋራ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም