የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ቦርድ ያዘጋጀውን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ቦርድ ያዘጋጀውን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዳማ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ቦርድ ያዘጋጀውን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ከግልና ከህዝብ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በተዘጋጀው የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ዙሪያ ማብራሪያ እየተሰጠ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፅዋዬ ሙሉነህ፤ ቦርዱ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያተኞችን የመመዝገብ፤ ፍቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ስራ እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በተለይም የኦዲት ሙያተኞች ሙያዊ ስነ ምግባር ጠብቀው እንዲሰሩ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
የውስጥ አስተዳደር፣ የአካባቢ፣ የንብረትና የፋይናንስ ኦዲትን ጨምሮ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አንስተው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በመተባበርም ወቅቱን የሚመጥን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የመድረኩም ዓላማ የሚዲያ ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች ስትራቴጂውን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠርና ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ለስትራቴጂው ውጤታማነት የሚዲያና ኮሙንኬሽን ባለሙያዎች ሚና የላቀ በመሆኑ ጉዳዩን በአግባቡ በመረዳት በተቋሙ ሁለንተናዊ ስራዎች የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።