የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት በዲጂታል ዲፕሎማሲ አማካኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት በዲጂታል ዲፕሎማሲ አማካኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የባህር በር መሻት በዲጂታል ዲፕሎማሲ አማካኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት፣ ማስተማርና ማሳወቅ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷም አልፎ ቀጣናውን በኢኮኖሚ ማስተሳሰር የሚያስችለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በጥራት ገንብታ አጠናቃለች፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ ቀጣናውን በሀይል የሚያስተሳስር፣ የታችኛው የተፋሰሱ አገሮችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የማይጎዳ ሜጋ ፕሮጀክት ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት በዲጂታል ዲፕሎማሲ አማካኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባል።
በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚፃረሩ ኃይላትን በዲጂታል ዲፕሎማሲ መመከት እንደሚገባም ተናግርዋል።
ኢትዮጵያ ሌሎችን ሳትጎዳ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት በተሳሳተ መንገድ የሚቀሰቅሱ ሀይሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እውነታውን በተገቢው መጠን እያስረዱ የተሳሳተውን አስተሳሰብ መመከት እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ ባሻገር የባህር በር መሻቷን ለዓለም ለማስተዋወቀ አዲስ አጀንዳ ይዛ መምጣቷን ገልጸዋል፡፡
የባህር በር ጉዳይ ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየ አጀንዳ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ በባለብዙ እና ሁለትዮሽ መድረኮች ያስመዘገበችውን ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የሚያደበዝዝ የሀሰት ትርክት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ዜጎች የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዲጂታል ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን አዎንታዊ ፍላጎት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት፣ ማስተማርና ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡