በቻን ውድድር በምድብ ሁለት ታንዛንያን ተከትሎ ማን ወደ ሩብ ፍጻሜ ያልፋል? - ኢዜአ አማርኛ
በቻን ውድድር በምድብ ሁለት ታንዛንያን ተከትሎ ማን ወደ ሩብ ፍጻሜ ያልፋል?

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከታንዛንያ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሶስቱ የምድብ ጨዋታዎቿ ሽንፈት ያስተናገደችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛ ከውድድሩ መሰናበቷ ይታወቃል። የዛሬው ጨዋታ መርሃ ግብር ከማሟላት የዘለለ ትርጉም የለውም።
በተቃራኒው ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ምድቡን የምትመራው ታንዛንያ አስቀድሞ ለሩብ ፍጻሜ መግባቷ የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ታንዛንያ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል።
በሌላኛው የምድብ ሁለት መርሃ ግብር ቡርኪናፋሶ ከማዳጋስካር በተመሳሳይ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በአማኒ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቡርኪናፋሶ በሶስት ነጥብ አራተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ከውድድሩ መሰናበቷ ይታወቃል።
በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማዳጋስካር ጨዋታውን ካሸነፈች ተመሳሳይ ነጥብ ይዛ ሁለተኛ ደረጃን የያዘቸውን ሞሪታኒያን በግብ ክፍያ በልጣ ለሩብ ፍጻሜ ታልፋለች።
በአንጻሩ ማዳጋስካር ነጥብ ከጣለች ሞሪታኒያ ታንዛንያን ተከትላ ሩብ ፍጻሜውን ትቀላቀላለች።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ብቸኛ ግንኙነታቸው እ.አ.አ በ2020 በዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉት ሲሆን ቡርኪናፋሶ 2 ለ 1 አሸንፋለች።