ቀጥታ፡

ሴቶች ችግሮችን የመፍታት ጥበቦቻቸውን በመጠቀም በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል- ኮሚሽኑ

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 10/ 2017(ኢዜአ)፡-  ሴቶች ችግሮችን የመፍታት ጥበቦችን በመጠቀም በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

''የሴቶች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጰያ'' በሚል መሪ ሀሳብ ሴቶችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን እንዳመለከቱት፤ የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማፅናት ችግሮችን  በመመካከር መፍታት ይገባል።

ለዚህም ሕዝብን በነቂስ ባሳተፈ መንገድ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት በኮሚሽኑ በኩል እየተከናወኑ ነው  ብለዋል።

በምክክር ሂደቱ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተለይም ሴቶች ችግሮችን በጥበብ የመፍታት እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን ተጠቅመው በምክክሩ ሂደት በመሳተፍ ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

በሚፈጠሩ ግጭቶች ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አንስተው፤ ስለሆነም ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች ድምፅ በተሟላ መንገድ እንዲካተት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሴቶች በሂደቱ ኮሚሽኑን እያገዙ አጀንዳቸውን በማስመዝገብና በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍ ለምክክሩ ሰኬታማነት እያገዙ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም ሴቶችን የማሳተፍ ተግባር እንደሚጠናከር ጠቅሰው፤ለምክክር ሂደቱ መሳካት መላ ኢትዮጵያውያን ሚናቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነሯ መልዕክት አስተላልፈዋል።በመድረኩ የሴት አደረጃጀት አመራሮችና አባላት እየተሳተፋ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም