በምክክር የሀገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር የሀገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- ወጣቶች
ባሕርዳር፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፡- በምክክር የሀገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የባሕርዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
''የወጣቶች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች በምክክር የሀገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ከወጣቶቹ መካከል በላይነህ ደጉ፤ ችግርን በምክክር መፍታት የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ በመሆኑ ይህንኑ መንገድ በመከተል ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ብሏል።
ከግጭትና ጦርነት ኪሳራ እና ጉዳት እንጂ የሚገኝ ትርፍ የለም ያለው በላይነህ፤ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር መፍታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አንስቷል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማገዝና የምክክር ሂደቱ አጋዥ በመሆን የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብሏል።
ሌላኛዋ ወጣት ፌቨን ሃይሉ ኮሚሽኑ በምክክር የሀገር ችግር እንዲፈታ በሂደቱ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ እየሰራ መሆኑን አድንቃ ይህንኑ መልካም እድል ለመጠቀም እንሰራለን ብላለች።
በመሆኑም ለምክክር ሂደት መሳካት እኔን ጨምሮ ሁላችንም ወጣቶች የድርሻችንን ለመወጣት መዘጋጀት አለብን ብላለች።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ሙሃመድ ሁሴን፤ ችግሮችን ለመፍታት መመካከር ወሳኝ ከመሆኑም ባሻገር በዚህ ሂደት የእኛ የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን፤ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው ወጣቶችን በማሳተፍና የምክክሩ አካል የማድረግ ጥረቱም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
የምክክር ሂደቱን የበለጠ ጠንካራና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች በሃገር ውስጥና በውጭ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው አዳዲስ የሚጨመሩ ሃሳቦች ካሉ እንደሚካተቱ ተናግረዋል።
በመድረኩ ወጣቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ኮሚሽኑ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ላይ ገለጻና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡