በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ሊገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ሊገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዲጂታል የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ሥርዓት እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።
አዲስ አበባ ከወረቀት የተላቀቀ አገልግሎትን ለመገንባት የስማርት ሲቲ ጉዞ ላይ ናት፤ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ የተለያዩ ዲጂታል አሰራሮችን ጀምሯል፡፡
የቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዳኛቸው ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ማዘመን የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡
ቢሮው የትራንስፖርት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በቬሎሲቲና በከተማ አውቶብሶች መጀመሩን ጠቅሰው፤ ተቋማቱ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የብዙኃን ትራንስፖርት የሚሰጡ የከተማ አውቶብሶችን ጨምሮ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አብዛኛው ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡
በስማርት ካርድ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሙ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስማርት ካርድ መጠቀማቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ከማስቻሉ በላይ ከእንግልት መዳናቸውን አንስተዋል፡፡
ካነጋገርናቸው ተጠቃሚዎች መካከል ሲሳይ ብርሃኑ፤ እንዳለችው ስማርት ካርድ መጠቀሟ በየዕለቱ ትኬት ለመቁረጥ የምታደርገውን እንግልት ቀንሶላታል።
መታፈሪያ ኃይሉና ትዕግስት ይጥና በበኩላቸው፤ ስማርት ካርድ መጠቀማቸው ያለሰልፍ በቅድሚያ እንዲስተናገዱና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
አመለወርቅ ሞሴ በበኩሏ አገልግሎቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የሰልፍ መጨናነቅ ያስቀረና በወር አንድ ጊዜ ካርድ በመሙላት ወጪዋን በአግባቡ እንድታስተዳድር እየጠቀማት መሆኑን አንስታለች፡፡
የቬሎሲቲ ባስ ካፒቴኖች በበኩላቸው፤ የስማርት ካርድ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የባስ ካፒቴን ሮማን አሰፋ እንዳለችው፤ አገልግሎቱ ለተጠቃሚውና ለእነሱ ጊዜን በመቆጠብ የምልልስ መጠንን እንዲጨምሩ እያደረገ ነው፡፡
የባስ ካፒቴን ዳኜ ካሳ በበኩሉ፤ አገልግሎቱ ለተጠቃሚዎች እና ለአሽከርካሪዎች ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ለስራቸው ቅልጥፍና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግሯል፡፡