የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ሊቨርፑል ቦርንማውዝን 4 ለ 2 አሸንፏል።

ትናንት ማምሻውን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዲስ ፈራሚው ሁጎ ኢኪቲኬ በ37ኛው ደቂቃ የአዲሱን የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ ኮዲ ጋፕኮ በ49ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

አንቶዋን ሴሜንዮ በ64ኛው እና በ76ኛው ደቂቃ ያስቆጠራቸው ግቦች ቦርንማውዝን አቻ አድርጓል።

ተቀይሮ የገባው ፌዴሪኮ ኪዬዛ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ሊቨርፑልን ዳግም መሪ አድርጓል።በቀያዮቹ ማሊያ የመጀመሪያ የሊግ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የአምናው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሐመድ ሳላህ በ95ኛው ደቂቃ የማሳረጊያዋን ግብ አስቆጥሯል።

በጨዋታው ቀያዮቹ የተሻለ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። ይሁንና በተከላካይ ክፍል መስመራቸው ላይ ክፍተት ታይቷል።

ቦርንማውዝ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጋጣሚውን ፈትኖ አምሽቷል።

የቦርንማውዙ ዴቪድ ብሩክስ የሊጉን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል።

ውጤቱን ተከትሎ  የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ የውድድር ዓመቱን በድል አሐዱ ብሎ ጀምሯል።

በጨዋታው በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው ዲያጎ ጆታ ታስቦ አምሽቷል።

የእንግሊዝ ሊግ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም