ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዑለማዎች ምርጫ በስኬት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዑለማዎች ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ 2017 አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ፉአድ መሐመድ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የመጂሊስ ምርጫ በዑለማዎች ዘርፍ  ምርጫ በዛሬው እለት በመላ ሀገሪቱ ተከናውኗል፡፡

ኢዜአ ተከታትሎ የዜና ሽፋን ከሰጠባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ፉአድ መሐመድ የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሰብሳቢው በመግለጫቸው በክልሉ 3 ሺህ 720 መስጅዶች የዑለማዎች ዘርፍ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ 

ሕዝበ ሙስሊሙ በነቂስ ወጥቶ ፍጹም ሰላማዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይሆነኛል ያለውን ተወካይ መምረጡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምርጫው በተከናወነባቸው የድምጽ መስጫ መስጅዶች የምርጫ ሂደቱ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የገበያ ቀን መሆኑን ተከትሎ የዑለማዎች ዘርፍ ምርጫ ባልተካሄደባቸው 201 መሳጅዶች ነገ ቀጥሎ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ ሙስሊሙ ነገ በሚደረገው ቀሪ የዑለማዎች ዘርፍ ምርጫ እና  ነሃሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም  በሚደረጉ የምሁራን፣ የወጣቶችና የሴቶች ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም