ቀጥታ፡

የዑለማዎች ምርጫን ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ አካሂደናል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ የዑለማዎችን ምርጫ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ ማካሄዳቸውን በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላማዊ ማዕከል ምርጫ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ከጁምአ ሶላት በኋላ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት በሚገኘው የወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላማዊ ማዕከል ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀኃፊና የመስጅዱ ዋና ኢማም ሸህ ሁሴን በሽር፤ ምርጫ ሂደቱ ህዝበ ሙስሊሙ ኃይማኖታዊ የዑለማ መሪዎችን በቅርበት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ዑለማዎች ለህዝበ ሙስሊሙ በቅርበት የሚሰጡ አገልጋዮች ናቸው ያሉት ኢማሙ፤ የምርጫ ሂደቱም በየመስጅዶቹ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንገድ ኃይማኖታዊ ስርዓትን ተከትሎ የተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት በሚገኘው የወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላም ማዕከል የተካሔደው ምርጫም ግልጽና አሳታፊ በሆነ አግባብ መካሄዱን ተናግረዋል።

የምርጫ ሂደቱም ህዝበ ሙስሊሙ መንፈሳዊና ማህበራዊ አገለግሎትን በመስጠት ጥቅምና ፍላጎቱን ለማስከበር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላም ማዕከል የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ዋና አስፈፃሚ ሀሰን መሐመድ፤ ለምርጫው ስኬት ወጣቶችና ተባባሪ አካላት ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።


 

የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ግልጽ፣ አሳታፊና ፍትሕዊ በሆነ መንገድ መከናወኑ ህዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳቸውን ሃይማኖታዊ አገልግሎት በተገቢው መንገድ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ቦርድ ፀኃፊ አማን አብደላ፤ በክፍለ ከተማው መሳጅዶች የተካሄደው የዑለማዎች ምርጫ ፍትሕዊና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።


 

የምርጫው ሂደቱ አሳታፊ፣ ሰላማዊና ፍትሕዊ በሆነ አግባብ መካሄዱም ህዝበ ሙስሊሙ የሚፈልጋቸውን ኃይማኖታዊ አገልግሎቶች በማስገኘት ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላም ማዕከል የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ ታዛቢ ሀሰን ሀምደግባ ኢብራሒም፤ የዑለማዎች ዘርፍ የመጅሊስ ምርጫ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቅ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መልካም ብስራት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ ሂደቱን ጠብቆ የሚካሄደው የመጅሊስ የምርጫ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም