ቀጥታ፡

መንግስት የተቀመጡ ግቦችና ፖሊሲዎችን ለሚያሳኩ ለውጥ አምጪ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የተቀመጡ ግቦች እና ፖሊሲዎችን ለሚያሳኩ ለውጥ አምጪ ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባውን የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በቬይትናም የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ ባደረጉት ጉብኝት ከኩባንያው ፕሬዝዳንት ጋር የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

ማምረቻው በከፍተኛ ጥራት የማምረት አቅም የተላበሰና በዘመናዊ የማሽን ሥርዓት የሚሰራ መሆኑን አመልክተው፤ የምርት ውጤቱ ለማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

መንግስት እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ልምድ እና እውቀት ያላቸውን ኢንቨስተሮች የመሳብ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አቅም እና ልምድ ያላቸው ባለሀብቶች እውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን በመጠቀም ለመስራት እየመጡ መሆኑን ተናግረው፤ የሚመጡት ባለሀብቶች በቂ ገንዘብና ልምድ ያላቸው እና በሚደረግላቸው ከፍተኛ ድጋፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉም ጠቁመዋል።


 

በመንግስት የተቀመጡ ግቦች እና ፖሊሲዎችን ለሚያሳኩ ለውጥ አምጪ ፕሮጀክቶች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

እንደ ቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ሁሉ በሌሎችም ዘርፎችም መሰል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ሁለት ተጨማሪ ማምረቻዎች በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፤ ግንባታቸውም በመስከረም 2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል።


 

ከብዙ አገሮች ካለው የሶላር ፓናል አምራች ቦታዎች አንጻር ኢትዮጵያ የተሻለች መሆኗንም ተናግረዋል።

በኢነርጂ ዋጋ፣በሚቀርበው የተማረ የሰው ሀይል ብዛት እና ጥራት፣ በቦታ ምቹነት እና በመንግስት ፖሊሲ የምትወዳደርባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውንም አንስተዋል።

ዘመናዊነትን፣ እውቀትን፣ ትርፋማነትን እና ምርታማነትን በኢትዮጵያ ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መናገር፣ መምራትና ተከታትሎ ማስፈጸም የመንግስት መለያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም