የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎትና ልማታቸውን እንዲያፋጥኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎትና ልማታቸውን እንዲያፋጥኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎትና ልማታቸውን እንዲያፋጥኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የስማርት አዳማ ግቦች ውጤታማነት፣ ቀጣይ የከተማዋ የልማትና ዕድገት ጉዞ ሂደት ላይ ያተኮረ መፅሐፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተመርቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የአሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የተሰናዳው መፅሐፍ የክልሉን ከተሞች አራት የልማት ግቦችና ቀጣይነት አቅጣጫ የቃኘ ነው።
ይህም ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት፣ የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደማጣቀሻ የሚያገለግል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይ በክልሉ ከተሞች ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችሉ የ"ስማርት'' ከተሞችን ለመፍጠር ልምድ የሚወሰድበት ሃሳቦችን የያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የክልሉ መንግስት ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎትና ልማታቸውን እንዲያፋጥኑ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ መፅሐፉ ባለፉት አራት ዓመታት በከተማዋ ተግባራዊ የተደረገውን የስማርት አዳማ ኢንሼቲቭ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሻገር የሚያግዙ ጠንካራ ሀሳቦች የያዘ ሰነድ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የስማርት አዳማ ግቦችን ለማሳካት የመሬት ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀምን በማዘመን ሀብቱን ከምዝበራ መታደግ መቻሉን አክለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመምራት ማዘመን ችለናል ያሉት ከንቲባው፤ በዚህም የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ከማሳደግ ባለፈ ብልሹ አሰራር መቀነስ ችለናል ብለዋል።
"ኢንተርፕሪነሮችን" ለማፍራት፣ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል ።
ዛሬ የተመረቀው መፅሐፍ የስማርት አዳማ ግቦችን ውጤታማ ጉዞ የቃኘ ከመሆኑም ባለፈ ከተማዋ በቀጣይ በሁለንተናዊ መልኩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማትና ዕድገት ላይ የተሻለ ለመስራት አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በመፅሐፉ ዝግጅት የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ኦሮሚያ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በተመሳሳይ ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ዘጠኝ የከተማ አውቶብሶች ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በዚህም አዳማ ከተማ አስተዳደር ስር መተዳደር የጀመሩ አዳዲስ ወረዳዎች ጭምር ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ የትራንስፖርት እጥረትን የሚቀንስ መሆኑ ተገልጿል።