የኡለማዎች ምርጫ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠርና ብቁ አመራሮችን ለማፍራት የላቀ ትርጉም አለው -ሸህ አብዱልከሪም ሸህ በድረዲን - ኢዜአ አማርኛ
የኡለማዎች ምርጫ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠርና ብቁ አመራሮችን ለማፍራት የላቀ ትርጉም አለው -ሸህ አብዱልከሪም ሸህ በድረዲን

ወልቂጤ፤ ነሐሴ 9/ 2017 (ኢዜአ) :- የኡለማዎች ምርጫ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠርና ብቁ አመራሮችን ለማፍራት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ አብዱልከሪም ሸህ በድረዲን ገለጹ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ መስጅዶች የኡለማዎች ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሸሕ አብዱልከሪም ሸሕ በድረዲን፤ በክልሉ ቀቤና ልዩ ወረዳ በዘቢሞላ ሃድራ መስጅድ በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ከዚሁ መርሃ ግብር በኋላ ባስተላለፉት መልእክትም የኡለማዎች ምርጫ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠርና ብቁ አመራሮችን ለማፍራት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይሕንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝበ ሙስሊሙ በሁሉም ዘርፍ መሪዎቹን እንዲመርጥ አስገንዝበዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የጉራጌና የየም ዞን እና የቀቤና ልዩ ወረዳ ክላስተር ምርጫ አስፈፃሚ ቶፊቅ አጫሉ (ዶ/ር)፤ ምርጫው በተቀመጠው አሰራር እና ስርዓት ታዛቢዎች በተገኙበት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ሙሰማ በበኩላቸው፤ ታዛቢዎች በተገኙበት ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ምርጫው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።
በመስጅዶች ድምጽ የሰጡ መራጮችም ይበጀናል፣ ሕዝበ ሙስሊሙን ያገለግላል ላልነው ኡለማ ድምጽ ሰጥተናል ብለዋል።