የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጎለብት ምሁራን ገንቢ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጎለብት ምሁራን ገንቢ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል
ክልል ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ፍላጎት እና ምክክርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጎለብት ምሁራን ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተመላከተ።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እና በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አማካኝነት የሚዘጋጀው 44ኛው 'ጉሚ በለል' የውይይት መድረክ ''የፖለቲካ ስብራቶች ከትናንት እስከ ዛሬ'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ በአወያይነት የተሳተፉት በኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሽመልስ ሀይሉ ባነሱት ሐሳብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመሀል መንገድ የተከተለ ባለመሆኑ ለዘመናት የችግር መነሻ ሆኖ ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ ችግር ገጥሞት መቆየቱንና ልማትና እድገት እንዳይሳለጥ፣ ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋገጥ አድርጎ ቆይቷል ነው ያሉት።
ከችግሩ ለመውጣትም የጋራ ትርክት በመገንባትና የጋራ ተቋማትን በማጠናከር ጠንካራ አገር የመገንባት ሂደቱ ላይ ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።
በዚህ ወቅትም የዲጂታል ሚዲያ እና የድህረ እውነት ዘመን እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው ከዚህ አንጻር ህዝቡ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙን መግራት እንዳለበት አስረድተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን እየተካሄደ ባለው አካታች አገራዊ ምክክር ሂደት ተራርቀው የሚወቃቀሱ አካላት አንድ ላይ ተቀምጠው በመነጋገርና በመደራደር የጋራ አገር ለመገንባት መትጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለሂደቱ ስኬታማነትም የፖለቲካ ልሂቃን ቀረብ ብለው ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ መነሻ የውይይት ጽሁፍ ያቀረቡት ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የነበሩ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችና ስብራቶች የሀገርን የልማት እና የእድገት ጉዞ አደናቅፈዋል ይላሉ።
በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ባልተገራ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና በድህረ እውነት ምክንያት ችግሩ አድማሱን እያሰፋ መሆኑን አመልክተዋል።
ከችግሩ ለመውጣት የተጀመረው አካታች አገራዊ ምክክር ዋና መንገድ መሆኑን ጠቅሰው በምክክሩ በጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ አረዳድ መያዝ እና ለሁሉም የተመቸች አገር መገንባት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
ከሁሉም በላይ የጋራ ትርክት ግንባታን ማጠናከር፣ ዲጂታል ግንዛቤን ማሳደግ እና የምሁራን ውይይት መድረኮችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የአብሮነት ባህል ቢኖራትም ይህን አገር በቀል ባህል ስርዓታዊ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ውስንነቶች እንደነበሩ የጠቀሱት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ናቸው።
በዚህም ምክንያት ነጠላ ትርክቶች የበላይነት እንደያዙ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመግታት መደማመጥ፣ መወያየት እና በጋራ ትርክት ላይ በመመስረት ሁሉንም የመሰለች፣ ሁሉንም ያቀፈች አገር መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ የ'ጉሚ በለል' ውይይትም እዚህ ላይ አተኩሯል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሁሉም አካላት አገራዊ አንድነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ በመንቀሳቀስ የተሻለ የፖለቲካ ባህል መገንባት ይገባል ብለዋል።
ነጠላ ትርክትን መግታት እና የጋራ ትርክት ግንባታን ማጠናከር ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የፖለቲካ ምሁራን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።