ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የዑለማዎች ምርጫ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ ደረጃ የመጅሊስ ምርጫ ዛሬ በዑለማዎች ዘርፍ ምርጫ በአዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች መካሄድ ጀምሯል።


 

በዚሁ መሰረት የዑለማዎች ዘርፍ ምርጫ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የወሎ ሰፈር አቡ-ሑረይራ መስጅድና ኢስላማዊ ማዕከልም እየተከናወነ ነው።


 

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለዑለማዎች ምርጫ በአዳማ ከተማ  ሁዳ መስጂድ ተገኝተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት መልእክት መጅሊሱ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠርና ህዝበ ሙስሊሙን ለማገልገል እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የዛሬው ምርጫም ይህንኑ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የ2017 ዓ.ም መጅሊስ ምርጫ በ49 ሺህ 92 መስጅዶች 13 ሚሊዮን 151 ሺህ 889 ህዝበ ሙስሊም እንደሚሳተፍ ይጠበቃል። 

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም ድረስ የምሁራን፣ ወጣቶች ሴቶችና የስራ ማኅበራት ተወካዮች ምርጫ ይካሄዳል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ሂደቱን ጠብቆ የሚካሄደው የመጅሊስ የምርጫ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም