ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት የሚሆን የትብብር የፖለቲካ ባህልን እየገነባ ነው- ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት የሚሆን አካታችና የትብብር የፖለቲካ ባህል እየገነባ መሆኑን በ12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በተሞክሮነት ማቅረቡን የፓርቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በጋና አክራ የተካሄደውን 12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡  

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ለውጥ ያስመዘገባቸውን ስኬታማ ተሞክሮዎች በጉባኤው ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ለአገረ መንግሥት ግንባታ ቁልፍ መሰረት የሚሆን የወል ትርክት እየገነባ እንደሚገኝ ማንሳታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መስርተው በሀገር ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው የሚሰሩበትና የሚመካከሩበት የትብብርና የሀሳብ ፉክክር አውድ መፈጠሩም በመድረኩ ቀርቧል ነው ያሉት።

ለአብነትም ብልጽግና ፓርቲ በህዝብ ድምፅ አሸንፎ በመሰረተው መንግሥት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት ስልጣን ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ  በማድረግ ኢትዮጵያን በጋራ ለመምራት የወሰደውን ቁርጠኝነት አንስተዋል፡፡

ፓርቲው አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት እየገነባ መሆኑን ገልጸው፤ በፌዴራል መንግሥቱ የአስፈጻሚ አካል ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ሀምሳ በመቶ ማድረሱን በተሞክሮነት ማጋራቱን ተናግረዋል፡፡

በመደመር እሳቤ በመመራት አገርን በጋራ የማሻገር ስኬታማ ጉዞ ለአፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም