ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ በ2018 በጀት ዓመት የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የሃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም የማሰራጫ መስመሮችን ማሻሻልና ማዘመን፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት መስጠት፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማረጋገጥና የሃይል ጥራት ችግርን ማቃለል ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ 148 የገጠር ቀበሌዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ጋር በማገናኘት የኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ሰባት ቀበሌዎችን ከዋና የኃይል መስመር ውጭ በፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ለ155 የገጠር ቀበሌዎች የኃይል አቅርቦት ማሟላት ተችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም 600 ሺህ አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ በበጀት ዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

የኃይል ብክነትን በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር ነባር የኢነርጂ ቆጣሪዎችን በዘመናዊ ስማርት ቆጣሪዎች ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት በበጀት አመቱ 53 ሺህ 714 ስማርት ቆጣሪዎችን ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉን ነው የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ ከኢነርጂ ሽያጭና ከሌሎች የገቢ ማግኛ ምንጮች 63 ነጥብ 12 ቢሊየን ብር መገኘቱንም አክለዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ20 ነጥብ 65 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎችን መጨመር፣ የሰው ኃይልና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ማጠናከር የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለተጨማሪ የገጠር ቀበሌዎች የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ፣ ለአዳዲስ ደንበኞች አገልግሎት መስጠትና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት መጨረስም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም