ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኡለማዎች ምርጫ ድምፅ ሰጡ

አዳማ ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኡለማዎች ምርጫ ድምፅ ሰጡ።

ፕሬዚዳንቱ በአዳማ ከተማ ሁዳ መስጂድ በመገኘት ድምጽ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት መጅሊሱ ጠንካራ ኢስላማዊ ተቋም ለመፍጠር እና ህዝበ ሙስሊሙን ለማገልገል እየሰራ መሆኑን ገልጸው የዛሬው ምርጫም ይህንኑ አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።


 

በዚህም መሰረት በሀገሪቱ በዛሬው እለት የኡላማዎች ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ መሪዎቹን በሚመርጥበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በንቃት በመሳተፍ አደራን መወጣት እንደሚገባ ተናግረው እርሳቸውም በዚሁ መልኩ ድምጽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ መሆኑን ገልጸው የዑለማዎች ምርጫው በዚህ ደረጃ እንዲካሄድ የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድና በየደረጃው ያለው ኮሚቴ ላደረጉት ጥረትና ትብብር አመስግነዋል።


 

በቀጣይ እሁድም የድምፅ አሰጣጡ በወጣቶች፣ ምሁራን፣ ሴቶችና በማህበረሰብ ደረጃ የሚቀጥል በመሆኑ ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም