በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የ13ተኛ ቀን ውሎ የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ጊኒ ከአልጄሪያ ከቀኑ 11 ሰዓት ካምፓላ በሚገኘው ማንዴላ ብሄራዊ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድቡ ካደረገቻቸው ሶስት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ያገኘችው ጊኒ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ተጋጣሚዋ አልጄሪያ ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
ማሸነፍ ለሁለቱ ሀገራት ለሩብ ፍጻሜ ለመግባት ያላቸውን እድል ያሰፋል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 15 ጊዜ ተገናኝተው በተመሳሳይ ስድስት ስድስት ጊዜ ሲያሸንፉ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በ15ቱ ጨዋታዎች ሀገራቱ በተመሳሳይ 23 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በዚሁ ምድብ ምሽት ሁለት ላይ ኒጀር ከደቡብ አፍሪካ በማንዴላ ብሄራዊ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኒጀር በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዳ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ተጋጣሚዋ ደቡብ አፍሪካ ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በማግኘት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ኒጀር በውድድሩ ለመቆየት ያላትን ጭላንጭል ተስፋ ለማስቀጠል ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ግዴታዋ ነው።
በአንጻሩ ደቡብ አፍሪካ ካሸነፈች ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድሏን ታሰፋለች።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሁለት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
የቻን ውድድር በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል