ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ እያመረቱ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ እያመረቱ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ እያመረቱ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በቬይትናም የቶዮ የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካ በነበረን ጉብኝት እና ከኩባንያው ፕሬዝደንት ጋር በነበረን ውይይት የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫዎችን በሀገራችን ለማምረት ተስማምተን ነበር ብለዋል።
ዛሬ በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በነበረን ጉብኝት በፓርኩ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጪያዎችን እያመረቱ በመመልከታችን ደስታ ተሰምቶናል ሲሉም ገልጸዋል።
ማምረቻው በከፍተኛ ጥራት ከፍተኛ ምርት የማምረት አቅም የተላበሰና በዘመናዊ የማሽን ሥርዓት የሚሰራ ሲሆን የምርት ውጤቱ ለማኑፋክቸሪንግ የውጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል ብለዋል።
ሁለት ተጨማሪ ማምረቻዎች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ወደ ምርት የገባውን ማምረቻ ሥራ ሂደት ተመልክተናል ነው ያሉት።
ይኽ ሥራ እሴት የተጨመረባቸው እና ያስቀመጥናቸውን ግቦች እና ፖሊሲዎች የሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የኢንቨስትመንት ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።