ቀጥታ፡

በሀገሪቱ 148 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ሆነዋል - አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፡- በ2017 በጀት ዓመት በሀገሪቱ 148 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የሃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ለአብነትም የማሰራጫ መስመሮችን ማሻሻልና ማዘመን፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት መስጠት፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማረጋገጥና የሃይል ጥራት ችግርን ማቃለል ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ በበጀት ዓመቱ 148 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከ500ሺህ በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከኢነርጂ ሽያጭና ከሌሎች የገቢ ማግኛ ምንጮች 63 ነጥብ 12 ቢሊየን ብር ማግኘቱንም አክለዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 ነጥብ 65 በመቶ እንድገት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም