ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያስመዘገበችው ስኬት የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔን እንድታስተናገድ አስችሏታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት የተመሰረተ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት ያስመዘገበችው ስኬት ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ለማስተናገድ ተመራጭ እንዳደረጋት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

በዚህም በብዝኃ ኢኮኖሚ መርህ ለአካባቢ ደኅንነት መሰረት የሆነ ስኬታማ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ አሻራ የልማት መርሃ ግብሮች በመቅረጽ ሰፋፊ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

ለአብነትም የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የፀሐይና የነፋስ ኃይል፣ የባዮ ጋዝ ፕሮጀክቶችና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ መገለጫዎች ናቸው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምትገነባው የኢኮኖሚ ሥርዓት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ ላይ የተመሰረተ ነው።

በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሰረተ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረትም የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መከላከል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ለማስተናገድ ተመራጭ እንዳደረጋት ተናግረዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገው ጥረትም የግብርና ምርታማነትን እያሳደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስምምነትን መነሻ በማድረግ የተቀረጸው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ "የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎችን ማፋጠንና የአፍሪካን የአረንጓዴ ልማት በገንዘብ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም