ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ መጤ አረም የመከላከል ተግባር ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ነው - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ መጤ አረም የመከላከል ተግባር ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ነው - ባለስልጣኑ

ባሕር ዳር፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፡- ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ መጤ አረምና ሌሎች ችግሮች የመከላከል ተግባር ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
ጣና በውስጡ የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎችን ጨምሮ ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግ የጎላ ፋይዳ ያላቸው ገዳማትና ቅርሶች የሚገኙበት ሐይቅ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም በዙሪያው ለሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በዓሣ ማስገር ስራ፣ ቱሪስቶችን በጀልባ በማጓጓዝና በሌሎች ዘርፎች በመሰማራት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ ተስፋሁን አለምነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሐይቁ እምቦጭ አረምን ጨምሮ ሌሎች መጤ አረሞች፣ በደለል የመሞላት ስጋትና ከከተሞች ቆሻሻ ፍሳሽ የመለቀቅ አደጋ እያጋጠመው ነው።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአካባቢውን ማሕበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ ተነድፎ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በተለይም ለሐይቁ ስጋት የሆነውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል ማህበረሰቡን በማስተባበርና ማሽኖችን በመጠቀም የማስወገድ ተግባር መቀጠሉን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የሐይቁን አካል ከወረረው የእምቦጭ አረም ውስጥ የሰው ሃይልና ማሽን በመጠቀም 2ሺህ 600 ሄክታር ያህሉን ማስወገድ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
አረሙን በማስወገድ ስራ ከ9 ሺህ በላይ የሰው ሃይል ማሳተፍ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ አረሙ ካለው በፍጥነት የመራባት ባህሪ አንፃር አሁንም የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ሐይቁን በደለል ከመሞላት ስጋት በዘላቂነት ለመጠበቅ በዙሪያው እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።
ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ሐይቁ የሚለቁ ተቋማትንም በመለየት አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው፤ የባሕር ሸሽ እርሻን ለማስቆም ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።
እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሐይቁ ደህንነት በመጠበቅ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ጣና ሐይቅ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ምንጭ የሆነ ትልቅ የሀገር ሃብት በመሆኑ በአግባቡ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የግድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።