በአዲስ አበባ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ያማከሉ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እየተገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ያማከሉ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ያማከሉና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በስፋት እየተገነቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ኃላፊ በላይ ደጀን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ስፖርት መልካም ስብዕና ያለው፣ በአካል፣ በአዕምሮና በስነ ልቦና ብቁና ንቁ የሆነ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ስፖርት ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብና አብሮነትን በማጎልበት ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ስፖርት ለስራ ዕድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ቢሮው መሰረተ ልማትን ለማስፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአራት ዓመት በፊት በከተማዋ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከአራት መቶ እንደማይበልጡ አስታውሰው፥ ለመሰረተ ልማት ግንባታ በተሰጠው ትኩረት አሁን ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ 1ሺህ 530 መድረሳቸውን አንስተዋል።
ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ያማከሉና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ለእግር ኳስ እና አትሌቲክስ ስፖርት ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ስፍራዎች በአሁኑ ጊዜ የቅርጫት፣ የእጅና የመረብ ኳስ፣ የጠረጴዛና ግራውንድ ቴኒስ የስፖርት ዓይነቶችን እንዲያካትቱ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡
የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለታዳጊዎችና ወጣቶች ስፖርታዊ ብቃት መዳበር ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ፥ ከተማዋ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንድታስተናግድ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ነዋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ እድል መፍጠራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ይህም አብሮነትን ባህል ያደረገ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያግዝ ከመሆኑም ባለፈ ብቁና ንቁ ዜጋን በመፍጠር የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ እውን የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ጎን ለጎን ቢሮው ታዳጊ ስፖርተኞች ማፍራት ላይ ትኩረት ማድረጉንም ቢሮ ሀላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
በከተማው ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ጉለሌ 03 ሜዳ ስፖርት ማዘውተሪያ አንዱ ነው፡፡
ታዳጊ ፅዮን ዋሲሁን እና እስጢፋኖስ ፀጋዬ ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ በአቅራቢያቸው መገንባቱ የስፖርት ክህሎታቸውን ለማሳደግ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 አፍንጮ በር ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ያገኘናቸው ታዳጊ ሱዴት ነሱር እና ብሩክ መንግስቱ በበኩላቸው ምቹና ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ መኖሩ የእግር ኳስ ህልማቸውን ለማሳካት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።