የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የወጣባቸውን ታላላቅ ከዋክብት ይዞ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የወጣባቸውን ታላላቅ ከዋክብት ይዞ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዝውውር መስኮት የወጣው ወጪ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክብረ ወሰኖችን የሰባበረ ነው።
ክለቦች እስከ አሁን በአጠቃላይ ከሁለት ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ አውጥተዋል።
ፍሎሪያን ዊትዝ፣ ብራያን ምቡዌሞ፣ ቪክቶር ዮኬሬሽ፣ ማቲያንስ ኩንሃ፣ ሁጎ ኢኬቲኬ እና ቤንጃሚን ሴስኮ ብዙ ገንዘብ ከወጣባቸው ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሊቨርፑል እና ቼልሲ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ በቀዳሚነት ስፍራ ላይ ተቀምጠዋል።
ዘንድሮ የሊጉ ክለቦች ያወጡት ረብጣ ገንዘብ አዲሱን የውድድር ዓመት የበለጠ አጓጊ እና ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል እና ቦርንማውዝ በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሮውን ያገኛል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት በኮሙዩኒቲ ሺልድ ፍጻሜ በክሪታል ፓላስ በመለያ ምት ተሸንፎ ዋንጫ ማጣቱ ይታወቃል።
ቀያዮቹ እንደ ሁጎ ኢኪቲኬ፣ ፍሎሪያን ዊትዝ እና ጀርሚ ፍሪምፖንግ ያሉ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ያለው የተከላካይ መስመር ክፍተት ዋንኛ ስጋቱ ሆኗል።
ቡድኑ የማጥቃት አቅሙን እንዳጠናከረው ሁሉ የተከላካይ ክፍሉን ጠንካራ ማድረግ እንዳለበት እየተገለጸ ይገኛል።
ቦርንማውዝ ዲን ሀውሰን፣ ኢሊያ ዛባርኒይ እና ሚሎስ ኬርኬዥን መሸጡ የተከላካይ ክፍሉን አሳስቶታል።
በአንቶዋን ሴሜንዮ፣ ኢቫኒለሰን እና ኤመርሰን የሚመራው የፊት መስመር በፈጣን መልሶ ማጥቃት የሚየያደርገው እንቅስቃሴ ለተጋጣሚው ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 24 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 19 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ቦርንማውዝ 2 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የ46 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።