የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ አስዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የህዝብ ለህዝብ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ አስዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።

ሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ "ፕላንት ፍራተርኒቲ" መርሃ ግብር የተጀመረ ሲሆን፤ ወደ ፓኪስታን አቅንቶ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ተሞክሮ የሚያካፍለው የመጀመሪያው የወጣቶች ቡድን በዓድዋ ድል መታሰቢያ አሸኛኘት ተደርጎለታል።


 

በመርሃ ግብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ፣ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ፣ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን እንዲሁም የክንፉ አመራር እና አባላት ተገኝተዋል።

የወጣቶች ቡድኑ በፓኪስታን በሚኖረው ቆይታ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሚያከናውን ሲሆን፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በመድረኩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ኢንሼቲቭ ያላትን ተሞክሮ ሌሎች ሀገራት ማካፈል መጀመሯ ዲፕሎማሲውን ከማጠናከር ባሻገር ለየህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መጠናከር ጉልህ አስዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ወደ ፓኪስታን የሚያቀናው የወጣቶች ቡድንም ከችግኝ ተከላ ባለፈ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የማድረግ ድርብ ሃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በፓኪስታን ቆይታችሁ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ ልትሰሩ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው ዙር "ፕላንት ፍራተርኒቲ" መርሃ ግብር በስምንት የአፍሪካ ከተሞች ወጣቶች የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማካፈል ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ በይፋ በተጀመረው ሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር በተመሳሳይ ወጣቶች በስምንት የአፍሪካና ከአፍሪካ ውጭ ባሉ ሀገራት የአረንጓዴ ኢኒሼቲቭ ተሞክሮን እንደሚያካፍሉ አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተቀረጸው አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ሌላው ገጸ በረከት መሆኑን በመግለጽ።


 

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ተመሳሳይ ፈተናዎች የሚጋሩ በመሆናቸው በዚህ ላይ በጋራ መስራታቸው ውጤታማ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የምትቀስማቸው በርካታ ተሞክሮዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና ዙሪያ ፓኪስታን ልምድ ያላት መሆኑን ገልጸው፤ ይሄንን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም