የጃፓን ካራቴ ሾቶ ኢትዮጵያ ሻምፒዮና በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2017(ኢዜአ)፦ 4ኛው የጃፓን ካራቴ ሾቶ ኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከነሐሴ 16 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይደረጋል። 

ውድድሩን አስመልክቶ የጃፓን ካራቴ ሾቶ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በሻምፒዮናው ላይ በሁሉቱም ጾታዎች  ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 300 ስፖርተኞች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። አካል ጉዳተኞችም በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ። 

በታዳጊዎች፣ በወጣቶች እና አዋቂዎች የእድሜ ክልል የተለያዩ የውድድር አይነቶች ይደረጋሉ። 


 

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሙሉነህ ጎሳዬ የጃፓን ካራቴ ሾቶ ኢትዮጵያ ፌዴሬሽን የሚያካሂደው ሻምፒዮና ለሌሎች ውድድሮች ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ ሻምፒዮናው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። 

የጃፓን ካራቴ ሾቶ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ዘውዱ ሻምፒዮናውን የተሻለ እና ስኬታማ ለማድረግ የሚያስፈልገው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። 

ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

በሻምፒዮናው ሜዳሊያ የሚያገኙ ስፖርተኞች የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ከኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ የሚነገርለት የጃፓን ካራቴ ሾቶ ባህላዊ እና ዘመናዊ ስልትን አጣምሮ የያዘ የካራቴ ስፖርት አይነት ነው።

ስፖርተኞች ለረጅም ጊዜ ጽንተው የሚቆዩባቸው የአቋቋም አይነቶች (Stances)  ፣ የሽንጥ ተለዋዋጭ እንቅስቃሴ እና በፍጥነት ስልቶችን መቀያየር (ካታ) የስፖርቱ ዋንኛ መገለጫ ባህሪያት ናቸው። 

ካራቴ ሾቶ ለስብዕና ግንባታ እና ጤና አጠባበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጸሉ።
 
ስፖርቱ በዓለም ደረጃ በዓለም አቀፉ ካራቴ ፌዴሬሽን፣ በሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን እውቅና ያገኘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም